By Mikael Sisay
Tigrai Onlne - May 19, 2014
አሁን…አሁን እንደሚሰማው ከሆነ የግብጽ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር ውይይት ለማድረግ እንፈልጋለን የሚል አስተያየት መስጠት ጀማምረዋል። ቀደም ሲል ይካሄድ የነበረውን የሦስትዮሽ ምክክር አሻፈረኝ ብላ ውይይቱን ያቋረጠችው ራሷ ግብጽ ነበረች፡፡
በተለያዩ አገራት እየተዘዋወረች ኢትዮጵያ ላይ ለማሳደም ያደረገችው ጥረት እንደከሸፈባት ግብጽ ሳትረዳ አልቀረችም፡፡ ትክክለኛው መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር መወያየትና ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም መከተልን እንደሆነ ከልብ በመገንዘብ ከሆነ ይበል የሚያስብል ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ የአባይ ተፋሰስ 3 ነጥብ 37 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን ይሸፍናል። ይህ የአፍሪካ አህጉርን 10 በመቶ የሚሆነውን መሬት ማለት ነው። የአባይ ወንዝ በተፋሰሱ ዙሪያ ያሉትን አገራት ሁሉ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል በቂ አቅም አለው። የሁሉንም የአባይ ተፋሰስ አገራት የልማትና የእድገት ጥያቄ መመለስ የሚችል የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ለዚህ ግን በቀጠናው ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋትን የግድ ይላል።
በተፋሰሱ ዙሪያ ያሉ አገራት ለጋራ ጥቅም የልማት ትብብራቸውን ማጎልበት ይጠይቃል። የአባይ ተፋሰስ መንግስታት በሚያደርጉት ሠላማዊና ልማታዊ ትብብርም ቀጠናውን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር በተፋሰሱ የሚኖሩት 160 ሚሊዮን ሕዝብም ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል።
ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀምንና አስተዳደርን በአስተማማኝ መንገድ መዘርጋት የተፋሰሱን የላይኛውም ሆነ የታችኛው አገራት ህዝቦችን ተጠቃሚ ከማድረጉ ጎን ለጎን በቀጠናው ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ያስችላል።
ሠላም በአስተማማኝ መልክ ሰፈነ ማለት ደግሞ የኢኮኖሚ ትስስሩ እየጠነከረ ስለሚሄድ ሁሉንም ወገን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደርጋል። ለዚህም ነው በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚገነባ ማንኛውም ዓይነት ልማት ማንኛውንም አገር አይጎዳም የሚባለው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብም ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንና ለግብጽም ጭምር መሆኑ እሙን ነው። ከዚህ በመነሳት ግብጽ አባይ ላይ የሚከናወኑ ልማቶች ይጎዱኛል በማለት ለዓመታት ስታራምደው የቆየችውና አሁን በቅርብ ጊዜ ብቅ ያደረገችው እምነትም ውኃ አለመቋጠሩን ለመገንዘብ አያዳግትም። ሥጋቱ ከተጨባጭ መነሻ በጥናት ተደግፎ የሚነሳ ሳይሆን ቀደም ሲል ከነበረው ብዥታ የመነጨ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
በቅርቡ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የአባይ ወንዝን በጊዜያዊነት ከተፈጥሯዊ መፍሰሻ መሥመሩ መቀልበሱን ተከትሎ ከግብጽ የተሰማው ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ በአዲስ መልክ የሰሞኑ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የግብጽ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ በአገሪቱ ከሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት እንዳስታወቁት የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ማንኛውንም ዓይነት አማራጭ ለመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ነው፡፡
ይህ ቀረርቶ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ኅብረተሰብ ያስደመመ ሁኔታ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተደመጠው በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በእጅ አዙር መጠቀም ሳይበጅ አልቀረም፡፡
ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትን በመደገፍና በማስታጠቅ ህዝቦች በሠላማዊ ሁኔታ እንዳይኖሩ ማበጣበጥ፣ በኢትዮጵያ በሚገኘው የግብጽ ኤምባሲ አማካይነት የስለላ ቡድን በማደራጀት የአገሪቱን ትላልቅ የልማት ተቋማትን በመለየትና በምን መልክ ማስተጓጎል እንደሚቻል በማጥናት ጥፋት መፈፀም የሚችል ቡድን እያደራጁ ሥምሪት ማድረግ የሚሉ ይገኙበታል።
እነዚህ አማራጮች ካልሰሩ ደግሞ የጦርነት አማራጭን የመጠቀምና ግድቡን ማፈራረስ የሚሉ ሃሳቦችን አቅርበው በይፋ ተወያይተዋል፡፡
ሆኖም ግን ከጊዜ በኋላ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በማየት ረጋ ብለው ሲያስቡት የነደፏቸው ሥልቶች በሙሉ የኢትዮጵያን ልማት ለማደናቀፍ እንደማያስችሉ በመገንዘብ ወደ ድርድር መምጣትን መርጠዋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እያደገችና እየፈረጠመች የመጣች አገር በመሆኗ፣ ሕዝቦቿ ልዩነት ውበታቸው መሆኑን በመገንዘብ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነታቸውን ያረጋገጡበት ወቅት በመሆኑ፣ አገሪቱ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ያላት ተሰሚነት እየጨመረ ስለመጣና ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት መልካም በመሆኑ እነዚህ የማተራመስ ሥልቶች እንደማያዋጡ የተገነዘቡ አንዳንድ የግብጽ ምሁራኖቻቸው ኢትዮጵያን ይቅርታ እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል።
ግብጻዊያኑ ይህንን ሁሉ ሲያቅራሩና ሲለፍፉ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በትዕግሥት ትከታተለው ነበር። አገሪቱ የጦርነት አማራጭን ተገዳ የምትወስደው ለመከላከል ብቻ እንጂ ለእብሪትና ለወረራ እንደማትጠቀምበት በሕገ መንግሥቷ በግልጽ አስፍራለች። በመሆኑም ግብጻዊያን እያነሱት ያለው ነገር አግባብ ባለመሆኑ በጥሞና ሊያዩትና ሊመረምሩት እንደሚገባ ደጋግማ አስታውቃለች፤ አሁንም ይህንኑ እያለች ነው።
አንድም የኢትዮጵያን ጥንካሬ በማየት በሌላ በኩል ደግሞ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በመረዳትና ከዚያም አልፎ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት በመገንዘብና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በማየት ከድርድር ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ እንደማይኖር በመረዳት ወደ ውይይት መምጣት እንደሚገባ አንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን ሳይቀሩ እየተናገሩ ነው።
ኢትዮጵያ በግብጽ በኩል የተፈጠረውን ጠብ አጫሪነት በትዕግሥት በማለፍ በግብጽ እየተነሳ ያለው ሥጋት ትክክል እንዳልሆነ የግብጽ ህዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ የተቻለውን ያህል ጥረት አድርጋለች።
ከታላቁ የህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ከማል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር መወያየታቸው በአወንታዊነት የሚታይ ነው።
ሁለቱ ባለሥልጣናት ባደረጉት ውይይት ከቀረርቶና ከእብሪተኝነት ይልቅ በጋራ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት በቀጣይ ምክክሩን ለማጠናከርና ለጉዳዩ ሠላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል የመነሻ ነጥብ አስቀምጠዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ መሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት ዘመናቸው ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት ግብጽ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ስላልነበራት ህዝቡ እርስ በርሱ በተበጣበጠበት፣ የመደራደርና የመከላከል አቅም ባልነበረው ወቅት ኢትዮጵያ አባይ ላይ ትልቅ ግድብ መገንባት ጀመረች የሚል ግንዛቤ እንዳያሳድር፤ ፀረ ልማት ኃይሎችም ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሊያናፍሷቸው በሚችሉ አሉቧልታዎች ውዥንብር እንዳይፈጠር በማሰብ ከግብጽ፣ ከሱዳንና ከኢትዮጵያ የተውጣጡ ባለሙያዎች ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ኤክስፐርቶች ጋር በመሆን የህዳሴው ግድብ በታችኞቹ አገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያመጣ፤ የግብጽ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ ህዝብም የኢትዮጵያ መንግሥት በጥናት ካረጋገጠው በተጨማሪ አለም አቀፍ ጥናቱን በማወቅ በተረጋጋ መልክ ልማቱ እንዲካሄድ ለማስቻል ጭምር የታለመ ነበር፡፡
በወቅቱ የግብጽ የህዝብ ዴፕሎማሲ ወኪሎችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ባደረጉት ውይይት እውነታውን ተገንዝበው መሄዳቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ጉዳይ ከተከናወነ ሁለት ዓመት ሆነው፡፡ አለም አቀፍ የኤክስፕርቶች ቡድንም በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ጥናትና ምርምር በማድረግ ከ700 ገጽ በላይ ሪፖርቱን አጠናቅሮ ለየአገራቱ አቀረበ፡፡
ሪፖርቱ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሌለም አስታወቀ፡፡ በዚህ መካከል ግንባታው እየተፋጠነ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንድ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ የአባይ ወንዝ በጊዜያዊነት ከተፈጥሯዊ ፍሰቱ መቀልበስና በሌላ መንገድ እስከተወሰነ ርቀት ሄደ መልሶ ወደ መስመሩ እንዲገባ የማድረግ ተግባር በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተከናወነ፡፡
ይህ ተግባር በኢትዮጵያን ይሰራል ተብሎ አይገመትም ነበር፡፡ አባይን ያህል ወንዝ ማስቀየስ ለኢትዮጵያውያን ኩራት ቢሆንም ከግብጽ ወገን በአንዳንድ ፖለቲከኞችና ምሁራን ዘንድ ነገሩ እንደ አዲስ አገርሽቶ አስፈላጊ ያልሆነ አስተያየት ማንፀባረቅ ተጀመረ።
ከመጀመሪያው አንስቶ በግብጽ ይነሳ የነበረው ሥጋት ኢትዮጵያ በአባይ ላይ መገንባት የሚቻለውን ትልቁን ግድብ ከሰራች ለግብጽ የሚመጣው የውኃ መጠን ስለሚቀንስ ህዝቤ ተጎጂ ይሆናል የሚል ነበር፡፡ ይህ እሳቤ በወቅቱም ተነስቶ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲራገብ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ከግብጽ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የግብጽን ህዝብ ማሳመን ችለው ነበር፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ የግብጽን ህዝብ የሚጎዳ ምንም ዓይነት ሥራ አይሰራም ብለው ነበር፡፡ አያይዘውም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለግብጽም ሆነ ለሱዳን የጎላ ጠቀሜታ ስለሚኖረው በጋራ ሰርተን በጋራ እንጠቀም የሚል መልዕክት ነበር ያስተላለፉት፡፡ ታላቁ መሪ ያቀረቡትን ሣይንሳዊ ትንተና ከሰሙት የግብጽ ምሁራንና ህዝብም ትክክል መሆኑን ያመኑ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህንን እምነታቸውን አሁንም ድረስ በተለያየ ሚዲያ እየገለጹ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ቀደም ሲል የነበረው ቃል እንደተጠበቀ መሆኑን በአጽንኦት በማስረዳት ላይ ይገኛል፡፡ ታላቁ የሕዳሴው ግድብ በሚገነባበት አካባቢ የሚለማ እርሻ የለም፡፡ በዚህ ግድብ የሚጠራቀመው ውኃም የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በስተቀር ለመስኖ ታስቦ እየተገነባ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አስታውቀዋል፡፡
ግብጽና ሱዳን ከዚህ ግድብ የሚያገኙት ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ግን ግብጻዊያን ወንድሞች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ መሠረት ሱዳን ወንዙ በሚሞላበት ጊዜ ለጎርፍ አደጋ ትዳረግ ነበር፡፡ ይህንን ለመከላከልና በአገሪቱ የሚከማቸውን ደለል ለማስወገድ ለውኃ ከምትይዘው ዓመታዊ በጀት 70 በመቶ የሚሆነውን ለዚሁ ተግባር ታውለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከተገነባ በኋላ ግን አገሪቱ ከችግሩ ትላቀቃለች። ሰባ በመቶ የሚሆነው የውኃ በጀቷን ለሌላ ልማት ማዋል ያስችላታል። ግብጽም ከተመሳሳይ ችግር እንድትላቀቅ እንደሚያስችል መረጃዎች ያሳያሉ።
የአባይ ውኃ ከዓመት ዓመት እኩል መጠን የለውም፤ በክረምት አለቅጥ ይሞላል፣ በበጋ ይጎድላል፡፡ ከዚህ የተነሳ አገራቱ በቂ መጠን ያለውን ውኃ የሚያገኙት በዓመት አራት ወራት ብቻ ነው፡፡ በቀሪዎቹ ወራት የውኃው መጠን ስለሚቀንስ ሱዳንና ግብጽ የሚያገኙት የውኃ መጠንም ይቀንሳል፡፡
ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በኋላ ግን አገራቱ የተመጣጠነ የውኃ ፍሰት ከዓመት ዓመት ማግኘት ይችላሉ። የወንዞች ውኃ መጠን ቢቀንስም ወደ አገራቱ የሚፈሰው የውኃ መጠን በግድቡ ምክንያት መጠኑን እምብዛም አይቀንስም። ሌላው ደግሞ ግድቡ የሚሰራው በጥልቅ ሰርጥ ውስጥ በመሆኑ የውኃ ትነትን ይቀንሳል፡፡ የትነት መጠኑ በቀነሰ ቁጥር አገራቱ የሚያገኙት የውኃ መጠን ይጨምራል፡፡ ይህ ደግ የመስኖ ሥራቸውን አጠናክረው ለመሥራት ያግዛቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የመስኩ ባለሙያዎች እየሰጡት ያለ ማረጋገጫ ነው።
በጥቅሉ ሲታይ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ በግብጽና በሱዳን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አለመኖሩን መገንዘብ ይቻላል። ይልቁንስ ከላይ የተዘረዘሩትን ጠቀሜታዎችን ከማስገኘቱም በላይ አገራቱን ከብክለት ነጻ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል በርካሽ ዋጋ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ይችላል። በመሆኑም ግድቡን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከአፍራሽ እንቅስቃሴ በመራቅ ሦስቱም አገራት ለጋራ ፍትሃዊ እድገት በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
በርካታ ምሁራን የአባይ ውኃ የኢትዮጵያና የግብጽን የጋራ ጥቅሞች ማርካት የሚችል እንደሆነ ይታወቃል። ግብጽ ግን ይህንኑ መገንዘብ የቻለች አይመስልም። ቀድሞ ይዛው ከነበረው አቋም የተላቀቀች አለመሆኗ ካለው ሁኔታዋ መረዳት ይቻላል። የተፋሰሱ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ በውኃው እንዳይጠቀሙ በተቀናጀ አኳኋን የመሥራት ፖሊሲ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ የቆየውና አሁንም ልትደግመው የምትሻው በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ በአካባቢያችን ለነበረው አለመረጋጋት ምንጭ ግብጽ ነች ባይባልም ከዚሁ አለመረጋጋት ተጠቃሚ መሆኗ ስለሚታያት ግጭቶቹን በማቀጣጠልና በማባባስ ረገድ የበኩሏን አስተዋፅኦ ስታደርግ እንደቆየችው ሁሉ ይህንኑ የግምት ሥትራቴጂ በበለጠ ለማቀጣጠል ቆርጣ መነሣቷን ከሙርሢ ቤተ መንግሥት እና ከሙርሲ ተቃዋሚዎች መንደር የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ግምቷ ኢትዮጵያ በማያባራ ጦርነት ከተናጠች በልማት ላይ ማተኮር አትችልም፤ በድህነት ስለምትሰቃይ ለማልማት ብትፈልግም አትችልም፤ ስለሆነም በውኃው ሳትጠቀም ትቀራለች የሚል ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአባይን ውኃ ለመጠቀም የሚያስችላትን ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ባላት አቅም ሁሉ የተረባረበች ቢሆንም የማታ ማታ እንደማያዋጣ የተገነዘቡ ይመስላል። ግብጽ በአረቡ ዓለም ያላትን ተሰሚነት ተጠቅማ ማንኛውም የአረብ አገር በአባይ ውኃ ልማት ላይ ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳይሰጥ ለማድረግ ችላለች፡፡ የጥላቻና የጥርጣሬ መንፈስም እንዲጠናከር ጥረት አድርጋለች፡፡ ግብጽን የዜሮ ድምር አስተሳሰቧን ትታ ወደ ጋራ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንድትመጣ በኢትዮጵያ በኩል ተደጋጋሚ ጥሪ እየቀረበላት ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከድህነት መውጣት ካለባት የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ እንዳለባት በማስመር፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የራስዋን ፍላጎት ከማሟላት አልፋ ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና የሕዝብ ለሕዝብ ቅርርብ እንዲኖር ለማድረግ አቅዳ እየሰራች ነው፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግብጽን እንደማይጎዳት በተግባርም እያረጋገጠችና እየተናገረች ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት ወንዞቿን ሁሉ በአግባቡና የሌሎችን ጥቅም በማይነካ መልኩ ለመሥራት ስትነሳ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ አስቀምጣ ማለፍ እንዳለባትም በመገንዘብ ነው፡፡
ይኸውም ከላይ እንደተጠቀሰው ግብጽ የአባይን ውኃ በተመለከተ ስትከተል የነበረውን እርዳታና ብድር የማስከልከል ፖሊሲ ከውስጥ ፖለቲካዋና ሌሎች ችግሮቿ በመነሣት ማስከልከል የምትችልበት ዋስትና ባይኖርም አባይ ላይ የሚገነባውን ግድብ በራሳችን አቅም መሥራታችን ከዚያ በኋላ ያሉትን ግድቦች በራሳችን አቅም መሥራት እንደምንችል የሚያረጋገጥልን ነው፡፡
በዚህም መሠረት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከዳር ዳር ተነስተው ለዘመናት ቁጭት ብቻ ያተረፈላቸውን አባይ ለመገንባት ታጥቀው በመነሳት ድህነት ያንገሸገሻቸው መሆኑን አስመሰከሩ፡፡ ኢትዮጵያ ከያዘቻቸው ዐበይት አጀንዳዎች አንዱ በተናጠልም ሆነ በጋራ ልማትን ማረጋገጥ ነው። ይህንን ለማድረግ የሠላም ፋይዳ የጎላ መሆኑን በመገንዘብ በአገር ውስጥ፣ በቀጣናውም ሆነ በአህጉር ደረጃ ሠላም ይሰፍን ዘንድ ቀላል የማይባል መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ትገኛለች።
በማንኛውም የአካባቢው አገራት የሚከሰት አለመረጋጋትና የሠላም እጦት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሌሎች አጎራባች አገራት የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ጫና ቀላል አይደለም። የቀጠናው ህዝቦች በዋናነት መታገል ያለብን ድህነትን በመሆኑ ግብጻዊያን ያጋጠማቸውን ችግርም በሠላማዊ መንገድ መፍታት ይችሉ ዘንድ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው።
በግብጽ ህዝብ መካከል የተፈጠረው ግጭትና አለመግባባት በዘላቂነት መፈታት የሚችለው በግብጻዊያን ብቻ በመሆኑ ሌሎች አገራት ከጣልቃ ገብነት እጃቸውን ሊሰበስቡ ይገባል። ግብጽ ታላቅ ታሪክ ያለው ህዝብ አገር ነች። በመሆኑም ይህ ታላቅ ህዝብ በመደማመጥና በመቻቻል ችግሩን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሊፈታ ይገባል።
በቅርቡ ከሥልጣን የወረዱት ፕሬዚዳንት ሙርሲ ቀደም ሲል በአገሪቱ ከሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የህዝብን ጥያቄ ለማለዘብና በሳቸው ላይ ይነሳ የነበረውን አመጽ ለማብረድ ትኩረቱን ወደ ሌላ ጉዳይ እንዲያዞር ለማድረግ ያለመ እንደነበር የፖለቲካ ምሁራን ይተነትናሉ፡፡
በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡ ቢሆንም የግብጽ ህዝብ የሙባረክን አገዛዝ ገርስሶ በጣለበት ወቅት በአገሪቱ መስፈን አለበት ብሎ ያምንባቸው የነበሩ ዐበይት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መልስ አላገኙም፣ ፕሬዚዳንቱ በአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው ያመጡት ለውጥ የለም፣ በሚል የግብጽ ህዝብ ከፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል።
የሕዳሴው ግድብ እየተገነባ ያለው በሲርና እና በጉባ መካከል በመሆኑና አካባቢው በተራሮች የተከበበ ስለሆነ ምንም ዓይነት የመስኖ ሥራ ለመሥራት ስለማያመች የውኃ መጠኑ በግድቡ ምክንያት ሊቀነስ እንደማይችል በተደጋጋሚ የተናገረ ቢሆንም “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉ ግንባታው ከተጀመረ ከሁለት ዓመታት በኋላም ሙርሲ ይመሩት በነበረው መንግሥት አንዳንድ ባለሥልጣናትና ጥቂት የግብጽ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቃውሞ እንዳለ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ተስተውለው ነበር፡፡
የግብጽና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች እንደመሆናቸው አንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን ምንም ያህል በአረጀውና በአፈጀው የተዛባ መንገድ ቢጓዙ ይዋል ይደር እንጂ እውነታውን በትክክል የሚረዱ ግብጻውያን ድምጽ የበላይነቱን እየያዘ ሲመጣ ሁኔታዎች በትክክለኛው አቅጣጫ ሊጓዙ እንደሚችሉ ይታመናል።
በህዝብ አመጽና በወታደራዊ ኃይል ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የተገደዱት መሐመድ ሙርሲ ከአገሪቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች ጋር አድርገውት በነበረው ምክክር ላይ አንዳንድ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተለያዩ ሥልቶችን መጠቀም እንደሚገባ አስምረውበት ነበር።
ለምሣሌም በኢትዮጵያ የሚገኙትን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ማደናቀፍ ይቻላል የሚል አቋም ላይ ደርሰው ነበር፡፡ የግብጽ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ተጠቅመን የአገሪቱን ልማት እናደናቅፋለን ለማለት የደፈሩት ከምን ተነስተው ነው? የሚለውን ማየት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እንደ መድረክና አንድነት የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ አንዳንድ ክስተቶችን ተከትለው ችግር የማባባስ ተግባርን በተለያየ አጋጣሚ ሲፈጽሙ መስተዋላቸውን ምናልባትም የግብጽ ፖለቲከኞች እንደ አንድ መነሻ አድርገው ሊወስዱት ይችሉ ይሆናል፡፡
ከአገር ውጭ ሆነውም ሕገ መንግሥቱን ተፃረው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ አሸባሪዎች አገራዊ ስሜት የሌላቸው መሆኑ ሌላው መነሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እነዚህ ጥቂት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አልሸባብ ኢትዮጵያን ለመውረር በኢትዮጵያ ላይ የጅሃድ ጦርነት ባወጀበት ወቅትም ክህደታቸውን በይፋ አሳውቀው ነበር፡፡
አገሪቱ ወሣኝ ሁኔታ ሲያጋጥማት እየተሸበለሉ ከጠላቶቻችን ጎራ የሚሰለፉት እነዚህ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በእውነቱ ለህዝብ እንዳልቆሙ በራሳቸው መንገድ እርቃናቸውን ወጥተዋል፡፡ የሕዳሴው ግድብ የማን ሊሆን ኖሯል? ይህ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ይቀያየራል፡፡ በአንዲት ዴሞክራሲያዊት አገር የህዝቡ የፖለቲካ ሥልጣን በተረጋገጠበት አገር መንግሥት መቀያየሩ የግድ ነው፡፡ ኢህአዴግም ህዝቡ እስከመረጠው ብቻ ነው ሥልጣን ላይ የሚቆየው፡፡ አሁን እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ልማቶች የህዝብ ቅርሶች መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡
በሕዳሴው ግድብ ከእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች በስተቀር መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አባይን ያህል የተፈጥሮ ፀጋ ይዞ መራቡና መሰደዱ ለዓመታት ሲቆጫቸው የነበረ በመሆኑ አሁን እንደዚህ ዓይነት ልማት በአባይ ላይ ሲዘረጋ ልማቱን ዳር ለማድረስ በአንድነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ግብጻዊያኑ በአገር ውስጥ መግባባት ስለሌለ ብሔሮችንና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንጠቀማለን ሲሉ፣ መድረክም በኢትዮጵያ መግባባት የለም፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የግድቡ ባለቤቶች አይደሉም የሚል አቋም እያንፀባረቀ ነው።
እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች የተቋቋሙትና በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ መንግሥት በሰጣቸው መብት መሠረት የተፈጠረውን የብዝሃ ፓርቲ ሥርዓት በመጠቀም ነው፡፡ መብቱን እየተጠቀሙ ሥርዓቱን ከሕገ መንግሥት ተጻራሪ በሆነ መንገድ ለመሸርሸር መንቀሳቀሳቸው እጅግ ያስገርማል።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የግብጽ የፖለቲካ ድርጅቶች የሕዳሴውን ግድብ ለማደናቀፍ ልብ ለልብ የተናገኙ ቢመስሉም ግድቡ የህዝቡ በመሆኑ ማለፊያ መንገዱ ዝግ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለአንድነታቸው፣ ለነፃነታቸውና ለክብራቸው ላፍታ የማያመነቱ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ መድረክና አንድነትም ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞች ከሚያራምዱት አመለካከት ብዙም ባልተናነሰ መልኩ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎት ውጭ የሆነ ሀሳብ ሲሰነዝሩ መሰማታቸው የሚያሳዝን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የግብጽን ህዝብ የሚጎዳ ነገር ማድረግን አይፈልግም፡፡ አባይ የግብጽንም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችል አቅም ያለው የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በወንዙ የአቅሟንና ድርሻዋ ወይም የተጠቃሚነት መብቷ የሚፈቅድላትን ያህል ብታለማ እንኳ የግብጽን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይጎዳል ተብሎ አይገመትም፡፡ ሱዳንም ሆነች ግብጽ ከዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነታቸው በተጨማሪ ከዓመት ዓመት የተመጣጠነ ውኃ ማግኘት እንደሚችሉ ባለሙያዎች አረጋግጠዋል፡፡ የሱዳን መንግሥት ይህንን በመረዳት ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ ለመሥራት ፍላጎቱን እየገለፀ ይገኛል፡፡ በተጨባጭም ሁለቱ ሱዳኖች የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ከግብጽ የተነሳውን ሃሳብ አውግዘዋል፡፡ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራትም በተመሳሳይ መልኩ ሃሳባቸውንና አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ግብጽ የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችሉት በጋራና በእኩልነት መርህ ላይ ተመስርተው በትብብር አባይን መጠቀም ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ የአባይ ውኃ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በገጸ ምድሯ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ ለመጠቀም የሚከለክላት አንድም ዓለም አቀፋዊ ሕግ የለም፡፡ በአገሪቱ ያለው መንግሥትም ልማታዊ በመሆኑ የጀመረውን ልማት ዳር ለማድረስ ያለሳለሰ ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡